You are currently viewing በካሊፎርንያ የመጀመሪያው የሙስሊም ኢትዮጵያዊያን ማኅበር በእሳት ቃጠሎ የወደመበትን ማዕከል በድጋሚ ለማቋቋም የድጋፍ ማሰባሰብ ጀመረ

በካሊፎርንያ የመጀመሪያው የሙስሊም ኢትዮጵያዊያን ማኅበር በእሳት ቃጠሎ የወደመበትን ማዕከል በድጋሚ ለማቋቋም የድጋፍ ማሰባሰብ ጀመረ

  • Post author:
  • Post last modified:April 22, 2025
  • Post comments:0 Comments

· በ“ሚንበር ቲቪ” ዋና አስተባባሪት ዓለም አቀፍ የድጋፍ ማሰብሰብ በግንቦት ወር መጀመሪያ ለማድረግ በዕቅድ ይዟል

በሰሜን አሜሪካ ካሊፎርንያ ግዛት በቤይ ኤሪያ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የቤይ ኤሪያ ሙስሊም ኢትዮጵያን ማኅበር (Ethiopian Bay Area Muslims Association – EBAMA)፤ ባለፈው ዓመት መጨረሻየወደመበትን ማዕከል በድጋሚ ለማቋቋም የድጋፍ ማሰባሰብ በይፋ አስጀምሯል፡፡

ማኅበሩ የድጋፍ ማሰባሰቡን በይፋ ያስጀመረው በዚህ ሣምንት ነው፡፡ እ.አ.አ ከ2001 አንስቶ ከ20 ዓመታት በላይ ለኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የዕውቀት እና የተርቢያ ማዕከል በመሆን ያገለገለው ማዕከሉ፤ “በድንገተኛ የእሳት ቃጠሎ”ውድመት የደረሰበት ባለፈው ዓመት ነሐሴ 2016 (ሴፕቴምበር 5/2024) ነው፡፡ ከዚህ ክስተት በኋላ በአካባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ያለ ማዕከል መቅረታቸውን በሥፍራው የሚኖረውና የድጋፍ ማሰባሰቡ አስተባባሪ የሆነው ዕውቁ ገጣሚ ኑረዲን ኢሳ ለ“ሚንበር ቲቪ” ተናግሯል፡፡

እንደ አስተባባሪው ከሆነ፤ ማዕከሉ በተለይ በዲን ጉዳይ በዋነኝነት በሕፃናት ላይ ትኩረት በማድረግ ከኢትዮጵያ ለዚሁ ተግባር ወደ አሜሪካ እንዲሄዱ በተደረጉ ኡስታዝ፤ የቂርኣት ፕሮግራም እንዲሁም ሣምንታዊ የዳዕዋ ፕሮግራም ያዘጋጅ ነበር፡፡ በዚህም በርካታ ሕፃናት የቁርኣን ጥናት ሲያጠናቅቁ ሌሎች ደግሞ ሒፍዝ ቀጥለዋል፡፡

ከዲን ተግባራት በተጨማሪ ሴቶች እና አረጋዊያን ማኅበራዊ ግዴታዎችን የሚወጡበት ማዕከሉ፤ የረመዳን ኢፍጣር ፕሮግራም፣ ዘላቂ የቀብር ሥፍራ አገልግሎት የሚሠጥ ነበር፡፡ በአሜሪካ ከሚሰጠው አገልግሎት ባሻገር በኢትዮጵያ በማኅበራዊ ዘርፍ ለሚንቀሳቀሱ የበጎ አድራጎት ማኅበራት ድጋፍ አድርጓል፡፡ ድጋፉ ተፈጥሮአዊ አደጋ በሚያጋጥምበት ጊዜ ምላሽ መስጠትን የሚያካትት ነው፡፡

የእሳት ቃጠሎው መነሻ በምርመራ ላይ የሚገኘውን ማዕከል በአሁኑ ሰዓት በድጋሚ በማቋቋም አገልግሎቱን ለማስቀጠል የገቢ ማሰባሰብ ፕሮግራሙይፋ ሲደረግ፤ በአጠቃላይ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን ኑረዲን ተናግሯል፡፡ በአጠቃላይ ከሚያስፈልገው
የገንዘብ መጠን በአባላት መዋጮ እስካሁን ድረስ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር እንደተሰበሰበ በመግለጽ፤ ይፋ የተደረገው ዘመቻ ቀሪውንመጠን ለማሰባሰብ በማቀድ የተደረገ መሆኑንም አአስረድቷል፡፡

በዚህ ሣምንት ይፋ የተደረገው የድጋፍ ማሰባሰብ በኦንላይን ገንዘብ መሰብሰቢያው ‘ጎ
ፈንድ ሚ’ የሚደረግ መሆኑን የገለጸው አስተባባሪው፤ በቀጣይ ግንቦት 2/2017 (ሜይ 5/2025) ዓለም አቀፍ የድጋፍ ማሰብሰብፕሮግራም እንደሚያዘጋጅ ጠቁሟል፡፡ ይህ የድጋፍ ማሰባሰብ በ“ሚንበር ቲቪ” ዋና አስተባባሪነት የሚደረግና ለስድስት ሰዓታት በተከታታይ የሚቆይ እንደሚሆንም ተናግሯል፡፡ በዚህ መርሐ ግብር ላይ “በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች የሚገኙ ሙስሊም ማኅበራት፣ በሌሎችም ዓለማትየሚገኙ የሙስሊም ጀመዓዎች ምላሽ እንዲሰጡ” ጥሪ አቅርቧል፡፡

የቤይ ኤሪያ ሙስሊም ኢትዮጵያን ማኅበር (EBAMA)፣ በቤይ ኤሪያ ለሙስሊሙ ማኅበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት የተመሠረተ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ነው። (ሚንበር ቲቪ)

Leave a Reply